የተከራይ ማሻሻያ ፕሮግራም
የተዘመነበት ቀን 2/17/2026
በሲያትል ውስጥ የሚገኙ አነስተኛ ንግዶችን ለመደገፍ በ2026 የተከራይ ማሻሻያ ፕሮግራማችን ሁለት ዓይነት የሽልማት ጥቅሎችን በማቅረባችን ደስተኞች ነን። ግባችን ንግዶች ከምልክቶች እና መሳሪያዎች ጋር የተያያዙ የፋይናንስ ተግዳሮቶቻቸውን እንዲቀርፉ መርዳት ነው። የምልክት እና የመሣሪያ ሽልማት ጥቅሎች ንግዶች አገልግሎታቸውን ለማስፋት እና ገቢያቸውን ለማሳደግ የሚረዱ አስፈላጊ ዕቃዎችን የመተካት ወይም መሣሪያዎችን የማሻሻል ወጪን ይሸፍናሉ።
ለምልክት ወይም ለመሣሪያ ሽልማት ጥቅል ከማመልከትዎ በፊት እባክዎን ከዚህ በታች ያሉትን ሙሉ የብቁነት መስፈርቶች እና ዝርዝሮችን ይመልከቱ።
የመረጃ ክፍለ ጊዜ
ስለዚህ የገንዘብ ድጋፍ ዕድል ለማብራራት እና ጥያቄዎችን ለመመለስ የመረጃ መድረኮች ይኖራሉ። የሚከተሉት ምናባዊ ክፍለ ጊዜዎች በWebex ላይ ይስተናገዳሉ እንዲሁም ይቀዳሉ፦
- ማክሰኞ፣ የካቲት 24፣ ከጠዋቱ 10 – 11:30 ሰዓት፦ የምዝገባ አገናኝ።
ማመልከቻዎች በቅርቡ ይከፈታሉ.
ወደ አንድ ክፍል ዝለል
የብቁነት መስፈርቶች
እነዚህን ሁሉ መስፈርቶች በሙሉ ካሟሉ ንግድዎ ለድጋፍ ብቁ ይሆናል፦
- ለትርፍ የሚሠራ፣ በግል የተያዘ ንግድ ነው (ፍራንቻይዝ ወይም ቼን አይደለም)።
- ለሕብረተሰቡ ጉልህ ጥቅም ይሰጣል (ለምሳሌ፣ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ ዝግጅቶችን መደገፍ ወይም ምግብ መለገስ)።
- ቢያንስ ለሁለት ዓመታት በሥራ ላይ ቆይቷል።
- ቢያንስ ለሶስት ዓመታት የንግድ ወይም የኢንዱስትሪ ልምድ አለዎት።
- ንግድዎ ቀኑ ያላለፈበት የሲያትል ከተማ ንግድ ፈቃድ አለው።
- የከተማውን የንግድ እና የሥራ ግብር ከፍለዋል።
- ሁሉንም ግብሮች ሙሉ በሙሉ ከፍለዋል ወይም ለሽልማቱ ከተመረጡ በሁለት ወራት ውስጥ ይከፍላሉ።
ንግድዎ የሚከተሉትን የአካባቢ እና የመጠን መስፈርቶች ማሟላት አለበት፦
- ንግድዎ በሲያትል ከተማ ወሰን ውስጥ ይገኛል።
- ሁለት (2) ወይም ከዚያ በታች ያሉ ቦታዎችን ነው የሚያንቀሳቅሱት።
- ንግድዎ ከ50 ያነሱ የሙሉ ጊዜ ተመጣጣኝ ሠራተኞች አሉት።
- ንግድዎ ከ$2 ሚሊዮን በታች ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢ አለው።
ለተከራይ ማሻሻያ ፕሮግራም ለማመልከት ብቁ ያልሆኑ ንግዶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
- ባልተቋቋመ (ያልተወሃዱ) የኪንግ ካውንቲ ውስጥ የሚገኙ ንግዶች
- በሲያትል ማዘጋጃ ቤት ህግ አንቀጽ 6.270 ስር የሚተዳደሩ "የአዋቂዎች መዝናኛ" ንግዶች።
- 501(c)(3)፣ 501(c)(6) ወይም 501(c)(19) ለትርፍ ያልተቋቋሙ አካላት
የምልክት ጥቅል
የምልክት ጥቅል (እስከ $15,000 የሚደርስ የጥሬ ገንዘብ ሽልማት)
ይህ የገንዘብ ሽልማት የተቋቋመን ንግድ አዲስ የውጭ ምልክቶችን ለመግዛት ሊረዳው ይችላል።
- ይህ ሽልማት ለንግድዎ የውጭ ምልክቶች መግዣነት ጥቅም ላይ መዋል አለበት።
- ይህ ሽልማት ምልክቶችን መትከልን አይሸፍንም።
- ተሸላሚዎች ለጉልበት እና የመትከያ ወጪን ለመክፈል የሚያስችል አቅም እንዳላቸው ማረጋገጥ አለባቸው።
- ለዚህ ሽልማት ለመታጨት አመልካቹ የብቁነትን፣ የአካባቢን እና የንግድ መጠንን በተመለከተ ሁሉንም ደንቦች ማሟላት አለበት።
- ንግዱ የሽልማት ውል ከተፈረመ በሶስት (3) ወራት ውስጥ ተከላውን መጀመር መቻል አለበት።
የመሣሪያ ጥቅል
የመሣሪያ ጥቅል እስከ ($50,000 የሚደርስ የጥሬ ገንዘብ ሽልማት)
ይህ የገንዘብ ሽልማት ለነባር ንግድ መሣሪያዎችን በመግዛት ሊረዳው ይችላል።
- መሣሪያዎች ከንግድ ዕቃዎች አቅራቢዎች መገዛት አለባቸው።
- ለዚህ ሽልማት ለመታጨት አመልካቹ የብቁነትን፣ የአካባቢን እና የንግድ መጠንን በተመለከተ ሁሉንም ደንቦች ማሟላት አለበት።
- ንግዱ የሽልማት ውል ከተፈረመ በሶስት (3) ወራት ውስጥ ተከላውን መጀመር መቻል አለበት።
የማመልከቻ ሂደት
ማመልከቻዎች ሰኞ፣ ኤፕሪል 13፣ 2026፣ ከምሽቱ 5 ሰዓት ላይ መቅረብ አለባቸው።
ማመልከቻዎን በኦንላይን ፖርታል በኩል ይላኩ። ከቀነ ገደቡ በኋላ የሚላኩ ማመልከቻዎች ከግምት ውስጥ አይገቡም።
አስፈላጊ ቀኖች
- ሰኞ፣ ማርች 2፣ 2026፦ የተከራይ ማሻሻያ ፕሮግራም ማመልከቻ ፖርታል ይከፈታል።
- ሰኞ፣ ኤፕሪል 13፣ 2026፦ የተከራይ ማሻሻያ ፕሮግራም ማመልከቻ ከምሽቱ በ5 ሰዓት ያበቃል
- ጁን 2026፦ የተመረጡ አመልካቾች ማሳወቂያ ይደርሳቸዋል እና ተጨማሪ መረጃ ማቅረብ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።
በሌሎች ቋንቋዎች ድጋፍ ይገኛል
ሁለት ቋንቋ የሚናገሩ ሠራተኞች በሚከተሉት ቋንቋዎች ጥያቄዎችን መመለስ እና አመልካቾች ማመልከቻቸውን እንዲሞሉ መርዳት ይችላሉ፦ አማርኛ፣ ቻይንኛ፣ ኮሪያኛ፣ ሶማሊኛ፣ ስፓኒሽ፣ ታይኛ እና ቬትናምኛ።
የትርጉም አገልግሎቶችን ለመጠየቅ፣ በ(206) 684-8090 ይደውሉ እና የሚከተለውን መረጃ በድምጽ መልዕክት ላይ ያስቀምጡ፦
- ስም
- ስልክ ቁጥር
- ተመራጭ ቋንቋ
- የሚፈለገው የቋንቋ ድጋፍ ዓይነት (የቅጽ ትርጉም፣ በስልክ ትርጉም ወዘተ)
የ2026 የተከራይ ማሻሻያ ፕሮግራም ማመልከቻዎን በቋንቋዎ ለመሙላት በአካል ቀርበው እርዳታ ለማግኘት፣ እባክዎን አጋሮቻችንን በሌክ ሲቲ ኮሌክቲቭ (Lake City Collective) ያግኙ።
- ሌክ ሲቲ ኮሌክቲቭ ማዕከል (Lake City CollectiveCenter)፦ 13525 32nd Ave NE, Seattle, WA 98125
- ሰኞ፣ ረቡዕ እና አርብ ከጠዋቱ 8 ሰዓት እስከ ቀኑ 1፡00 ሰዓት፣ ወይም በቀጠሮ። እባክዎን በ((206) 701-1470 ይደውሉ።
የምርጫ መስፈርቶች እና የግምገማ ሂደት
የእኛ ቢሮ፣ በ Grow America ከሚገኙ አጋሮቻችን ጋር በመሆን ማመልከቻዎችን በማህበረሰቡ ላይ በሚያመጣው ተጽዕኖ፣ በፕሮጀክት ዝግጁነት እና በፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ላይ በመመስረት ገምግሞ ነጥብ ይሰጣል።
ለማመልከቻዎች ነጥብ ሰጥተን በሚከተሉት ሁኔታዎች ላይ ተመስርተን ለሽልማት ቅድሚያ እንሰጣለን፦
- ፍትሃዊነት፦ ለከፍተኛ መፈናቀል ስጋት የተጋለጡ ሰፈሮችን እና/ወይም በጥቁር፣ በተወላጆች፣ በቀለም ሰዎች ወይም በሴቶች ባለቤትነት የተያዙ ንግዶችን ለሚደግፉ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ እንሰጣለን።
- አዋጭነት፦ ጠቅላላ ሽያጮችን፣ ገቢዎችን እና የቢዝነስ ባለቤትን ተሞክሮ በመመልከት ንግዱ ምን ያህል ጠንካራ እና ዘላቂ እንደሆነ እንመለከታለን።
- የፕሮጀክት ዝግጁነት፦ የቦታውን፣ የፕሮጀክት ዝርዝሮችን፣ በጀትን እና ከሌሎች የገንዘብ ምንጮች ቁርጠኝነት በመገምገም ፕሮጀክቱ ዝግጁ መሆኑን እናረጋግጣለን።
- ተፅዕኖ፦ ለማህበረሰቡ ጥቅም የሚሰጡ እና አዎንታዊ ለውጥ የሚያመጡ ፕሮጀክቶችን ወይም የንግድ ባለቤቶችን እንመለከታለን።
የመጨረሻ ተወዳዳሪዎች የእያንዳንዱን ፕሮጀክት አዋጭነት እና የፋይናንስ ፍላጎት ለመወሰን አስፈላጊውን የቦታ ጉብኝት እና ቃለ መጠይቅ ጨምሮ ለንግድ ስራቸው አዋጭነት ይገመገማሉ። እነዚህ እርምጃዎች ከተጠናቀቁ በኋላ ሽልማቶች ይፋ ይደረጋሉ።
ፕሮጀክቶች ድጋፍ ከተሰጣቸው በኋላ፣ ንግዶች የገንዘብ ድጋፉ እንዲቀጥልላቸው የሚከተሉትን ማቅረብ አለባቸው፦
- አምስት (5) ዓመታት ቀሪ ያለው ከአከራይ የተፈረመ የኪራይ ውል ወይም ተመጣጣኝ ሰነድ ለምሳሌ፦ የሁለት ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የተረጋገጠ የኪራይ ማራዘሚያ ያለው የሶስት (3) ዓመታት ቀሪ የኪራይ ውል።
- የሽልማት ውል ከተፈረመ በሶስት (3) ወራት ውስጥ ተከላ መጀመር።
የማመልከቻ ቁሳቁሶች
ማመልከቻዎን ከማስገባትዎ በፊት ለመዘጋጀት የሚከተሉትን ሰነዶች ይመልከቱ።
አስፈላጊ መረጃ
የሚከተለው ማስረጃ ከማመልከቻዎ ጋርመቅረብ አለበት፡-
- Unified Business Identifier (የተዋሃደ የንግድ መለያ) ቁጥር
- ንግዶች ለዋሽንግተን ስቴት የንግድ ፍቃድ ሲያመለክቱ ባለ 9 አሃዝ UBI ቁጥር ይቀበላሉ። ይህ በDepartment of Revenue (የገቢዎች ክፍል) በኦንላይን ወይም በፖስታ በኩል ሊከናወን ይችላል።
- እንዲሁም በኢንተርኔት ላይ ያለውን የUBI ቁጥር መፈለግ ይችላሉ።
- City Business License (የከተማ ንግድ ፈቃድ) ቁጥር
- በሲያትል ውስጥ የሚነግድ ማንኛውም ሰው ባለ 6 አሃዝ የሲያትል ንግድ ፍቃድ የግብር ሰርተፍኬት (የCity Business License በመባልም ይታወቃል)፣ የCity Customer (የከተማ ደንበኛ) ቁጥር ወይም አጠቃላይ የንግድ ፍቃድ ሊኖረው ይገባል። የንግድ ባለቤቶች ይህንን የምስክር ወረቀት በየአመቱ እስከ ታህሳስ 31 ድረስ ማደስ አለባቸው።
- ይህ የከተማ ንግድ ፈቃድ ቁጥር ከዋሽንግተን ስቴት የንግድ ፈቃድ የተለየ ነው። ቁጥርዎን በከተማ ንግድ ፈቃድ Find a Business (የንግድ ማግኛ) የፍለጋ መሣሪያ ላይ ማግኘት ካልቻሉ የዋሽንግተን ስቴት ፈቃድ ብቻ ሊኖርዎት ይችላል።
- ንግዶች ለከተማ ንግድ ፈቃድ ማመልከት እና በኢንተርኔት ላይ ወይም በፖስታ ማደስ ይችላሉ።
- የንግድ እና የሥራ ግብር ማስገባት
- ለተከራይ ማሻሻያ ፕሮግራም ለማመልከት ፍላጎት ያላቸው አነስተኛ ንግዶች ለዚህ ፈንድ ብቁ ለመሆን የከተማ ንግድ ፈቃድ እና የንግድ እና ሥራ የግብር መስፈርቶችን ማክበር አለባቸው።
- ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ባይኖርም ወይም ምንም ዓይነት የግብር ዕዳ ባይኖርብዎትም እያንዳንዱ ንግድ ለከተማው ማመልከት እና ሪፖርት ማድረግ አለበት። የሲያትል የንግድ ግብር ከዋሽንግተን ስቴት የንግድ ግብር ጋር አንድ አይደለም። ንግዶች የሲያትል ግብሮችን ከክልል ግብሮች ለይተው ማስገባት አለባቸው። ንግዶች በኢንተርኔት ላይ ወይም በፖስታ ማስገባት እና ሪፖርት ማድረግ ይችላሉ። ስለ እነዚህ ግብሮች ተጨማሪ ጥያቄዎች ካሉዎት፣ ንግዶች የሲያትል ፋይናንስን በ tax@seattle.gov ማግኘት ይችላሉ።
- ንግዶች ዓመታዊ ግብር የሚከፈልበት ጠቅላላ ገቢያቸው ከ100,000 ዶላር በታች ከሆነ አጠቃላይ የንግድ እና የሥራ ግብር ዕዳ የለባቸውም፣ ነገር ግን ንግዶች አሁንም ማስገባት አለባቸው።
- ለተከራይ ማሻሻያ ፕሮግራም ለማመልከት ፍላጎት ያላቸው አነስተኛ ንግዶች ለዚህ ፈንድ ብቁ ለመሆን የከተማ ንግድ ፈቃድ እና የንግድ እና ሥራ የግብር መስፈርቶችን ማክበር አለባቸው።
- የ2024 እና 2025 የፌዴራል ግብር መረጃ
- የ2025 ግብሮችዎን ካልሞሉ፣ እባክዎ የውስጥ የፋይናንስ መግለጫ ያስገቡ።
- ሶስት (3) ዓመታት ወይም ተመሳሳይ የማደስ አማራጮች የቀረው የተፈረመ የሊዝ ውል ።
- ከመሣሪያ/ምልክት አቅራቢዎች የቀረቡ የንግድ ተመኖች።
- የታቀደውን የሽልማት መጠን በፍላጎት ቅደም ተከተል የሚያስቀምጥ ዝርዝር በጀት ።
- የሽልማት ገንዘባቸውን ለማሟላት ለሕብረተሰቡ የሚሰጡትን የህዝብ ጥቅም የሚገልጽ መግለጫ። ይህ የተፈጠሩ ሥራዎችን፣ የተደገፉ ማህበረሰብ ዝግጅቶችን ወይም የተለገሱ ምግቦችን ለምሳሌ ሊያካትት ይችላል።
የገንዘብ ድጋፍ ውሎች
- የተከራይ ማሻሻያ ፕሮግራም ድጎማዎች ከ0% ወለድ ጋር እንደ ይቅር ሊባል የሚችል ብድር ይሰጣሉ። ብድሩ ወደ ስጦታነት የሚለወጠው ንግዱ የመጨረሻው የክፍያ መጠየቂያ ካስገባ ጀምሮ ለአንድ (1) ዓመት ሥራውን ከቀጠለ እና የሕዝብ ጥቅም መስፈርቶቻቸውን ካሟሉ በኋላ ነው።
- የተከራይ ማሻሻያ ፕሮግራም ሽልማት የፕሮጀክቱን ሙሉ ወጪዎችን አይሸፍንም። አነስተኛ የንግድ ሽልማት ተቀባዩ የፕሮጀክታቸውን የምልክት እና የመሣሪያዎች መትከያ ወጪ መሸፈን ይጠበቅበታል።
- ሽልማቶች ሽልማቱ ከተነገረበት ጊዜ ጀምሮ በሁለት ወራት ውስጥ ውል መግባት አለባቸው እና ሽልማቱ ውሉ ከተፈረመ በኋላ በስድስት (6) ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተከፍሎ ማለቅ አለበት።
በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎች
ብዙ ንግዶች ወይም ቦታዎች ቢኖሩኝስ?
ብዙ ንግዶች ካሉዎት ወይም ከሁለት (2) ያልበለጡ ቦታዎች ካሉዎት፣ ለአንድ ንግድ ወይም ለአንድ ቦታ አንድ (1) የገንዘብ ድጋፍ ሽልማት ብቻ ማመልከት ይችላሉ።
ተንቀሳቃሽ የምግብ ንግድ/ጋሪ እንደ አንድ ቦታ ይቆጠራል?
ከአንድ የቋሚ ቦታ ንግድ በተጨማሪ ጋሪ/ተንቀሳቃሽ ንግዶች መኖር፣ የተከራዩት የንግድ ቦታ ስላልሆነ ከሁለት (2) ያልበለጡ ቦታዎች መኖራቸው ለሚለው መስፈርት አይቆጠርም።
በገንዘብ ድጋፍ ጥያቄዬ ውስጥ ምን ማካተት አለብኝ?
የማመልከቻ መስፈርቱን የሚያሟሉ (በፍላጎት ቅድሚያ የተዘረዘሩ) ሙሉ የንግድ መሳሪያዎችን ዝርዝር ያካትቱ፣ እስከ ከፍተኛው $50,000 ጥያቄ ድረስ። ከተመረጡ በኋላ በጀትዎ ላይ መጨመር አንችልም፣ ስለዚህ እባክዎን ጊዜ ወስደው ትክክለኛ ዋጋዎችን ይሰብስቡ እና ለንግድዎ በእውነት የሚያስፈልጉትን ሁሉ ይጠይቁ።
ገንዘቡን ለምን መጠቀም እችላለሁ?
የገንዘብ ድጋፍዎን ከተፈቀደለት ነጋዴ የንግድ መሳሪያዎችን ለመግዛት ወይም የውጭ ምልክቶችን ለማሠራት ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
የመሣሪያዎቼ ዋጋ ምን ያህል እንደሚሆን የራሴን ግምት ማስገባት እችላለሁ?
አይ። ማመልከቻውን ሲያስገቡ ትክክለኛ የዋጋ ተመኖችን ከአቅራቢዎች/ምልክት ሠሪዎች ማግኘት ይጠበቅብዎታል።
የተከራይ ማሻሻያ ሽልማት በመኖሪያ ቤቴ ውስጥ ለሚገኝ የቤት ውስጥ ንግድ ገንዘብ መስጠት ይችላል?
አይ። የከተማው የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጠው በንግድ ቦታ ህንፃ ውስጥ ለሚገኙ ንግዶች ብቻ ነው።
ለስንት የሽልማት ጥቅሎች ማመልከት እችላለሁ?
በእያንዳንዱ የማመልከቻ ዙር በአንድ ጊዜ ለአንድ (1) ሽልማት ብቻ ማመልከት ይችላሉ። ቀደም ሲል የተሸለሙ ከሆነ፣ የሽልማት ዓይነት ምንም ይሁን ምን፣ በዚህ ዓመት ለማመልከት ብቁ አይሆኑም።
ማወቅ ያለብኝ ለገንዘብ ሽልማቶች የሚያስፈልጉት መስፈርቶች ምንድን ናቸው?
ሁሉም የገንዘብ ሽልማት ጥቅሎች የሚሰጡት 0% ወለድ ባለው ብድር መልክ ነው። እነዚህ ብድሮች የሚሰረዙ ናቸው እና የውሉን ደንቦች ካሟሉ መመለስ አይጠበቅባቸውም። የሚደገፉት በደመወዝ ወጪ ግብር በኩል ሲሆን ይህም ንግዶች በሠራተኛ ደሞዛቸው ላይ በመመስረት የሚከፍሉት የግብር አይነት ነው። ይህ የገንዘብ ምንጭ እንዲሰረዝ መከተል ያለባቸው ደንቦች አሉት። ከሚያስፈልጉት መስፈርቶች አንዱ "የተለመደው ደመወዝ" ሲሆን ይህም ማለት ሠራተኞች በሚሠሩበት ቦታ ፍትሃዊ እና መደበኛ ደመወዝ መከፈል አለባቸው ማለት ነው። እንዲሁም "ለህዝብ ጥቅም የሚሰጡ" መሆን አለባቸው፣ ይህም ፕሮጀክቱ ለሕብረተሰቡ አዎንታዊ ተፅዕኖ ማምጣት አለበት ማለት ነው። ሠራተኞቻችን እነዚህን መስፈርቶች ለማሟላት እቅድ በማውጣት ያግዙዎታል።
ሽልማቴን መሣሪያዎቼን ለመትከል ለመክፈል ልጠቀምበት እችላለሁ?
አይ፣ ገንዘቡ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችለው ከተመሰከረለት ሻጭ መሳሪያዎችን ለመግዛት ብቻ ነው። እነዚህን ገንዘቦች ለተከላ (installation) ሥራ መክፈያነት መጠቀም ‘አሁን ያለውን የሥራ ደመወዝ’ (prevailing wage) ሕግ እና የኢንዱስትሪና የሠራተኛ መምሪያ (L&I) ቁጥጥርን ያስከትላል። ይህ ከተገኘ፣ መልሰው እንዲከፍሉ ሊጠየቁ ይችላሉ።
የተከራይ ማሻሻያ ፕሮግራም የመምረጥ ሂደት የጊዜ መስመር ምን ይመስላል?
በ2026 አንድ የማመልከቻ ዙር ይኖረናል። የስድስት ሳምንት የማመልከቻ ጊዜ ካለቀ በኋላ፣ ከአጋሮቻችን ጋር በመተባበር፣ ማመልከቻዎችን መገምገም እና ተሸላሚዎችን መምረጥ እንጀምራለን። ከሰኔ 2026 ጀምሮ አመልካቾችን ስለ ውጤታቸው/ስለ ሁኔታቸው ማሳወቅ እንጀምራለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ለማመልከት ምን መረጃዎች ያስፈልጉኛል?
ዝርዝር የጥቅል መረጃ ለማግኘት ዋናውን ገጽ ይመልከቱ።
የማመልከቻውን የትርክት ጥያቄዎች እንዴት መመለስ አለብኝ?
እባክዎን በተቻለ መጠን ብዙ ዝርዝር መረጃ ያካትቱ። ይህ እንደ የንግድ ባለቤት ታሪክዎን እና በዙሪያዎ ያለውን ሰፈር እንዴት እንደሚደግፉ የመናገር እድል ነው። እባክዎን ግልጽ ይሁኑ እና ለጎረቤቶችዎ ወደፊት ምን ለማድረግ እንዳቀዱ ሳይሆን ከበፊትም ምን ሲያደርጉ እንደቆዩ ይንገሩን፣ ። ምሳሌዎች የሚቀንሱ ዋጋዎች ያሏቸው አገልግሎቶችን መስጠት፣ ለአረጋውያን ቅናሽ ማድረግ ወይም በአካባቢው የንግድ ማህበር ውስጥ መሳተፍን ያካትታሉ። ምናልባት ቦታዎን በነፃ ወይም በቅናሽ ዋጋ ለማህበረሰቡ፣ ለቡድኖች ሊያቀርቡ ወይም ሆን ብለው በአካባቢዎ ያሉ ወጣቶችን ሊቀጥሩ ይችላሉ። እነዚህ ምን አይነት መረጃ ማካተት እንዳለብዎት የሚያሳዩ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።
በማመልከቻው ላይ እገዛ ቢያስፈልገኝስ?
ስለ ማመልከቻው አጠቃላይ ጥያቄዎች ካሉዎት፣ እባክዎን ወደ oed_tiprogram@seattle.gov ኢሜል ይላኩ ወይም በ(206) 684-8090 ይደውሉ።
ስለ ማመልከቻው አጠቃላይ ጥያቄዎች ካሉዎት፣ እባክዎን ወደ oed_tiprogram@seattle.gov ኢሜል ይላኩ ወይም በ(206) 684-8090 ይደውሉ።
ጽ/ቤታችን ሁሉም ማህበረሰቦች የኢኮኖሚ ዕድሎችን እንዲያገኙ በማረጋገጥ በሲያትል ውስጥ ለሁሉም ሰው ተስማሚ የሆነ ተደራሽ እና ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ቁርጠኛ ነው።
የሲያትል ከተማ፣ እያንዳንዱን ሰው በፕሮግራሞቹ እና በእንቅስቃሴዎቹ እንዲሳተፍ ያበረታታል። እርዳታ፣ ትርጉም፣ ለአካል ጉዳተኞች የሚደረጉ ማስተካከያዎች ወይም በተለየ ቅርጸት የተዘጋጁ ሰነዶች ከፈለጉ፣ ቢሮአችንን በ(206) 684-8090 ወይም በOED@seattle.gov ያነጋግሩ።